call us now

251 911 23 08 57 / 60 76 06

Early child development

ልጆች አሁን በደረሱበት የእድገት ደረጃ ላይ የነበሩ አይደሉም፡-

ሕጻናት በለጋነታቸው ሙሉ በሙሉ የሌሎች ጥገኞች ነበሩ፡፡ አሁን ደግሞ ራሳቸውን መርዳት ፈልገዋል፡፡ በራሳቸው ዙሪያ ስለምትሽከረከረው ትንሿ ዓለም ጥቂት ነገሮችን ማወቅ ጀምረዋል፡፡ አሁን ያች ትንሽ ዓለም እየሰፋችና እየተለጠጠች መጥታለች፡፡ ይሁን እንጂ በአፀደ ሕጻናት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሕጻናት ስለራሳቸው ብቻ ስለሚያስቡና ማንኛውንም ነገር ከራሳቸው አንፃር ስለሚመለከቱ የራስ ወዳድነት (Ego-Centeric) ጠባይ ያጠቃቸዋል፡፡

አንድ ሕጻን አዘውትሮ የሚያንፀባርቃቸው ቃላት ራሱን ብቻ የሚወክሉ ለምሳሌ እንደ “እኔ”“የእኔ” የመሳሰሉ ናቸው፡፡ ሕጻኑ በለጋ እድሜው በራሱ ዙሪያ የሚገኝ ማንኛውም ነገር የእርሱ የግል ንብረት እንደሆነ ወይም የእርሱ መሆን እንደሚገባው አድርጎ ያስባል፡፡ ለምሳሌ “ይህ የእኔ ነው‹‹ይህ የእኔ ኳስ ነው››“እሷ የእኔ እናት ነች”፣ “ያን እፈልጋለሁ” የሚሉ አባባሎችን ደጋግሞ ይጠቀማል፡፡ የአፀደ ሕፃናት ከባቢ እነዚህን ባህርያት ማስተናገድ ይኖርበታል፡፡

በአንድ ወቅት እናት፣ አባትና የቅርብ ቤተሰብ አባላትን ብቻ ያካትት የነበረው ጠባብና ውስን አካባቢ አሁን ሰፋ ወዳለ አካባቢነት ተለውጧል፡፡ የአካባቢው መለወጥ በርካታ ሌሎች ሰዎች በአካባቢው መኖራቸውን እንዲያውቅና እንዲረዳ ማረጋገጫ ሆኖታል፡፡ ለምሳሌ መምህራን፣ ነርሶች፣ ጥበቃ ሰራተኞች፣ ፅዳት ሠራተኞች፣ አትክልተኞች ወ.ዘ.ተ መኖራቸውን እየተረዳ ነው፡፡ ሕጻኑ አሁን ለተጨማሪ አዳዲስ ሁኔታዎች ተጋላጭ ሆኗል፡፡ ከወላጆቹ ሌላ በት/ቤቱ ውስጥ ትልቅና ጎልማሳ የሆኑ መምህራንና እጅግ በርካታ አዳዲስ ፊቶች ያሏቸውን ሕጻናት ማየት ጀምሯል፡፡ የሕፃኑ ዓለም እየተቀያየረ መጓዝ ቀጥሏል፡፡ ባሕርይውም እንዲሁ እየተቀየረ ነው፡፡ እሱም ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር እራሱን የማስማማትና ማለማመድ ፈተናን እየተጋፈጠ በመጓዝ ላይ ነው፡፡ በአዲስ ሁኔታዎች በመዋጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሚያስተውላቸው ነገሮች፣ ሁኔታዎችና ክስተቶች ጋር እራሱን እያላመደ በእድገት ሂደት ላይ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሚከናወነው በተከታታይ በሚተገበር ሙከራና ልምምድ ነው፡፡ ካለተሞክሮ፣ ልምድና እውቀት እንዴት ሊገኝ ይችላል? ሕጻኑ ይጥራል፤ በአካባቢው የሚያገኛቸውን ነገሮች ይሞክራል፤ ይፈትሻል፤ ሁሉንም ለመመርመር ይጣደፋል፤ አዳዲስ ስኬቶችና ትንንሽ እውቀቶችን ወደ ስብስቡ ለማካተት ይጓጓል፤ ያገኛቸውን ነገሮች ይነካካል፤ ይዳስሳል፤ ያስተውላል፡፡ የሕጻኑ ሙከራና የመማሩ ሚስጥር ይሄው ነው፡፡ ሙከራውና ልምዱ በሕጻኑ እድሜ፣ የእድገት ደረጃ፣ ጤና፣ ባህልና ሰብዕና ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ መምህራንና ወላጆች ይህን የሕጻኑን አዳዲስ ነገሮች የሞሞከር ጥረትና የመለማመድ ፍላጎት በጥንቃቄ ተከታትሎ ማገዝ ተገቢ ነው፡፡

መልካም፣ መልካሙን ለሕጻናት!

ሳህሉ ባዬ

www.enrichmentcenters.org

 


  • SHARE IT ON

Comments

leave a comments

BECOME VOLUNTEER

“If our hopes of building a better and safer world are to become more than wishful thinking, we will need the engagement of volunteers more than ever.”