call us now

251 911 23 08 57 / 60 76 06

Two and three years old

የ 2 እና 3 ዓመት ሕጻናት ባህርያት፡-

እያንዳንዱ ሕፃን ልዩ በመሆኑ መወዳደር ካለበት መወዳደር ያለበት ከራሱ ጋር ብቻ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአጠቃላይ አፈራረጅ እያንዳንዱን የእድሜ ክልል የሚወክሉ መሠረታዊ ባሕርያት አሉ፡፡ የታዳጊ ሕጻናትን ባሕርያት፣ ፍላጐትና የእድገት ሂደት ስርዓት መረዳት ለእያንዳንዱ ክፍልና ለእያንዳንዱ ሕጻን ተዛማጅ የሆኑ ዓላማዎችን በቅደም ተከተል ነድፎ በመርሃ ግብር ማዘጋጀት ጠቀሚ ነው፡፡ ሕጻናት ወደ ትቤ/ት የሚሄዱበት የእድሜ ክልል እንደሚኖሩበት አካባቢ ይለያያል፡፡ በአንዳንድ አገሮች በሦስት፤ በአራት፤ በአምስትና በስድስት ዓመታቸው የሚጀምሩ ሲሆን በሌሎች አገሮች ደግሞ በሁለት ወይም በሦስት ዓመት እድሜ ይጀምራሉ፡፡ ሕጻናት በሁለት ዓመታቸው አዳዲስ ነገሮችን መማር እንደሚችሉ ባለሞያዎች ይገልጣሉ፡፡ በአካባቢያቸው የሚገኙ ነገሮችን ያስተውላሉ፡፡ ለአካላዊ እንቅስቃሴ የሚረዷቸውን መራመድንና መሮጥን ይለማመዳሉ፡፡ ከፍ ያሉ ነገሮችን በመያዝ መንጠላጠል ይጀምራሉ፡፡ እንዲህ፣ እንዲህ እያሉም ወደ ሦሰተኛ ዓመታቸው ይሸጋገራሉ፡፡

በሦስት ዓመት እድሜ አብዛኞቹ ሕጻናት ቢያንስ መሠረታዊ የመናገር ክሂሎት ስለሚኖራቸው የቃላት ክምችታቸው በየዕለቱ ይጨምራል፡፡ በዙሪያቸው ካሉ ሌሎች ሰዎች ጋር ቀስ በቀስ እየተግባቡ መስማማትና ነገሮች መመርመር፣ መፈተሸ፣ መሞከር፣ መጠንቆል፣ መቅመስ…ወ.ዘ.ተ ይጀምራሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች የሕጻኑን የማያቋርጥ ቀጣይ እንቅስቃሴ በመገንዘብ ይህን እድሜ  “የመገስገስ” እድሜ ይሉታል፡፡ በእርግጥ ይህ እድሜ ሕፃናት የመስማት፣ የመናገር፤ የማስተዋል፣ የመተባበር፣ የመረዳዳት ችሎታዎችንና የእኔነት ስሜቶችን ማዳበር የሚጀምሩበት እድሜ ነው፡፡ ሆኖም በዚህ እድሜ ክልል ሕጻናት የራስ ወዳድነት ባሕርይ ስለሚያጠቃቸው ከሌሎች ሕጻናት ጋር ለመጫወት ያላቸውን ዝግጁነት እምብዛም አያሳዩም፡፡ በዚህ ምክንያት ለብቻቸው የጎንዮሽ ጨዋታ መጫወትን ይመርጣሉ፡፡ በነፃነት መንቀሳቀስ ስለሚፈልጉ አንዳንዴ የአዋቂዎችን እርዳታ ይቃወማሉ፡፡ ወደ አራተኛ ዓመታቸው መሸጋገሪያ ላይ እንደ ግል ባሕሪያቸው ከገደባቸው የመውጣት አዝማሚያ ያሳያሉ፡፡ በመቀጠል ዓመት በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ ሕጻናት ተለዋዋጭ ለሆኑ የእድገት ሂደቶች ተገዢ በመሆን እርስዎን ለማስደሰት የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡ “አይሆንም/አይደለም” የሚባሉ የእምቢተኝነት ቃላት አሁን “አዎ/አቤት/እሺ” ወደሚሉ ጠቃሚ ቃላት የሚለወጡበት አራተኛ ዓመት የእድሜ ክልል ተሸጋግረዋል፡፡

 

መልካም፣ መልካሙን ለሕጻናት!

ሳህሉ ባዬ

www.enrichmentcenters.org

 


  • SHARE IT ON

Comments

leave a comments

BECOME VOLUNTEER

“If our hopes of building a better and safer world are to become more than wishful thinking, we will need the engagement of volunteers more than ever.”